1 ሕዝቅያስ እንዲህ ባለ ታማኝነት ነገሮችን ሁሉ ካከናወነ በኋላ፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ይሁዳን ወረረ። ድል አድርጎ የራሱ ሊያደርጋቸው በማሰብም የተመሸጉትን ከተሞች ከበበ።
2 ሕዝቅያስም ሰናክሬም መምጣቱንና ኢየሩሳሌምንም ለመውጋት ማሰቡን ባወቀ ጊዜ፣
3 ከከተማዪቱ ውጭ ያሉት የውሃ ምንጮች እንዲዘጉ ከሹማምቱና ከጦር አለቆቹ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ረዱት።
4 ብዙ ሰዎችም ተሰብስበው “የአሦር ነገሥታት መጥተው ስለ ምን ብዙ ውሃ ያገኛሉ?” በማለት ምንጮቹን ሁሉና በምድር ውስጥ ለውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ውሃ ዘጉ።
5 ከዚህ በኋላም ንጉሡ ጠንክሮ በመሥራት፣ ከቅጥሩ የፈራረሱትን ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ማማ ሠራበት፤ በውጭ በኩልም ሌላ ቅጥር በመገንባት የዳዊትን ከተማ ድጋፍ እርከን አጠናከረ፤ እንደዚሁም ብዙ የጦር መሣሪያዎችንና ጋሻዎችን ሠራ።