1 ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ።
2 እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳይል፣ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ።
3 በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ።
4 በእርሱም ትእዛዝ የበኣሊም መሠዊያዎችን አፈራረሱ፤ እርሱም ከበላያቸው የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎችን አደቀቀ፤ የአሼራን ምስል ዓምዶችን፣ ጣዖታቱንና ምስሎቹን ሰባብሮ ከፈጫቸው በኋላ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነ።
5 የካህናቱን ዐጥንት በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ፤ በዚህ ዐይነትም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ።