2 ዜና መዋዕል 35:2-8 NASV

2 ካህናቱን በየአገልግሎታቸው መደበ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎትም እንዲተጉ አበረታታቸው።

3 እስራኤልን ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩትና ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አላቸው፤ “የእግዚአብሔርን ታቦት የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ አኑሩ፤ በእናንተ ትከሻ አትሸከሙት፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ።

4 በእስራኤል ንጉሥ በዳዊትና በልጁ በሰሎሞን በተጻፈው መመሪያ መሠረት፣ እንደየቤተሰባችሁ በክፍል በክፍላችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ።

5 “ሌዋውያን ባልሆኑ ወንድሞቻችሁ አንጻር እንደየቤተ ሰቡ ምድብ በተቀደሰው ስፍራ ቁሙ፤ ለእያንዳንዱም የቤተ ሰብ ምድብ ሌዋውያን ይኑሩት።

6 ከዚያም የፋሲካውን በጎች እረዱ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ባዘዘውም መሠረት ዕርዶቹን ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።”

7 ኢዮስያስም እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆኑ ባጠቃላይ ሠላሳ ሺህ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺህ ወይፈን ከራሱ ሀብት ሰጠ።

8 ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ።