ሆሴዕ 10:1-7 NASV

1 እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤ብዙ ፍሬም አፈራ፤ፍሬው በበዛ መጠን፣ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤ምድሩ በበለጸገ መጠን፣የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ።

2 ልባቸው አታላይ ነው፤ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ። እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ያወድማል፤የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ያፈራርሳል።

3 እነርሱም፣ “እኛ ንጉሥ የለንም፤ እግዚአብሔርን አላከበርንምና፤ንጉሥ ቢኖረንስ፣ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?” ይላሉ።

4 ከንቱ ተስፋ ይሰጣሉ፤በሐሰት በመማል፣ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ስለዚህም ፍርድ፣በዕርሻ ውስጥ እንደሚገኝ መርዛማ ዐረም ይበቅላል።

5 በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤ሕዝቡም ያለቅስለታል፤በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤በምርኮ ከእነርሱ ተወስዶአልና።

6 ለታላቁ ንጉሥ እንደ እጅ መንሻ፣ወደ አሦር ይወሰዳል፤ኤፍሬም ይዋረዳል፤እስራኤልም ስለ ጣዖቱ ያፍራል።

7 ሰማርያና ንጉሥዋ፣በውሃ ላይ እንዳለ ኩበት ተንሳፍፈው ይጠፋሉ።