ሆሴዕ 4:1-7 NASV

1 በምድሪቱ በምትኖሩ በእናንተ ላይ እግዚአብሔር የሚያቀርበው ክስ ስላለው፣እናንት እስራኤላውያን ይህን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤“ታማኝነት የለም፤ ፍቅርም የለም፤እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድሪቱ የለም።

2 በዚያ ያለው ርግማን፣ መዋሸት፣ መግደል፣መስረቅና ማመንዘር ብቻ ነው፤ቃል ኪዳንን ሁሉ ያፈርሳሉ፤ደም ማፍሰስና ግድያ ይበዛል።

3 ስለዚህ ምድሪቱ አለቀሰች፤በውስጧም የሚኖሩ ሁሉ ኰሰመኑ፤የምድር አራዊት፣ የሰማይ ወፎች፣የባሕርም ዓሦች አለቁ።

4 “ነገር ግን ማንም ሰው አይከራከር፤ማንም ሌላውን አይወንጅል፤በካህናት ላይ ክስን እንደሚያቀርቡ፣ሕዝብህ እንደዚያው ናቸውና።

5 ቀንና ሌሊት ትደናበራላችሁ፤ነቢያትም ከእናንተ ጋር ይደናበራሉ፤ስለዚህ እናታችሁን አጠፋታለሁ፤

6 ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል።“ዕውቀትን ስለናቃችሁ፣እኔም ካህናት እንዳትሆኑ ናቅኋችሁ፤የአምላካችሁን ሕግ ስለ ረሳችሁ፣እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ።

7 ካህናት በበዙ ቊጥር፣በእኔ ላይ የሚያደርጉት ኀጢአት በዝቶአል፤ክብራቸውንም በውርደት ለውጠዋል።