ሚልክያስ 1:10-14 NASV

10 “በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቊርባን አልቀበልም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

11 ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

12 “እናንተ ግን የእግዚአብሔር ገበታ፣ ‘ርኩስ ነው’ ምግቡም፣ ‘የተናቀ ነው’ በማለት ታቃልላላችሁ።

13 ደግሞም፣ ‘ይህ ድካም ነው’ በማለት በንቀት ጢቅ አላችሁበት ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።“በቅሚያ የመጣውን፣ አንካሳውንና የታመመውን እንስሳ ቊርባን አድርጋችሁ ስታቀርቡ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላል እግዚአብሔር፤

14 “በመንጋው ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተባዕት በግ ኖሮት ይህንኑ ሊሰጥ ተስሎ ሳለ በማታለል ነውር ያለበትን እንስሳ ለጌታ የሚሠዋ ርጒም ይሁን፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።