1 በመጨረሻው ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተራራ፣ከተራሮች ልቆ ይታያል፤ከኰረብቶች በላይ ከፍ ይላል፤ሕዝቦችም ወደ እርሱ ይጐርፋሉ።
2 ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤“ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንሂድ፤በመንገዱ እንድንሄድ፣መንገዱን ያስተምረናል።”ሕግ ከጽዮን ይመጣል፤ የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም።
3 እርሱ በብዙ ሕዝብ መካከል ይፈርዳል፤በሩቅና በቅርብ ባሉ ኀያላን መንግሥታት መካከል ያለውን ግጭት ያቆማል፤ሰይፋቸውን ማረሻ፣ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጉታል።አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም።
4 እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤የሚያስፈራቸው አይኖርም፤ የእግዚአብሔር ጸባኦት አፍ ተናግሮአልና።
5 አሕዛብ ሁሉ፣በአማልክቶቻቸው ስም ይሄዳሉ፤እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም፣ከዘላለም እስከ ዘላለም እንሄዳለን።