ሰቆቃወ 2:10-16 NASV

10 የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች፣በምድር ላይ በዝምታ ተቀምጠዋል፤በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ፤ማቅም ለበሱ፤የኢየሩሳሌም ወጣት ሴቶች፣ራሳቸውን ወደ ምድር ዝቅ አደረጉ።

11 ዐይኔ በለቅሶ ደከመ፤ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤ልቤም በሐዘን ፈሰሰች፣በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣ሕዝቤ ተደምስሰዋልና፤ልጆችና ሕፃናት ደክመዋልና።

12 በከተማዪቱ መንገዶች ላይ፣እንደ ቈሰሉ ሰዎች ሲደክሙ፣በእናታቸው ክንድ ላይ፣ነፍሳቸው በመውጣት ላይ ሳለች፣“እንጀራና የወይን ጠጅ የት አለ?”እያሉ እናቶቻቸውን ይጠይቃሉ።

13 የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፤ ስላንቺ ምን ማለት እችላለሁ?ከምንስ ጋር አወዳድርሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፤አጽናናሽ ዘንድ፣በምን ልመስልሽ እችላለሁ?ቍስልሽ እንደ ባሕር ጥልቅ ነው፤ማንስ ሊፈውስሽ ይችላል?

14 የነቢያቶችሽ ራእይ፣ሐሰትና ከንቱ ነው፤ምርኮኛነትሽን ለማስቀረት፣ኀጢአትሽን አይገልጡም።የሚሰጡሽም የትንቢት ቃል፣የሚያሳስትና ከመንገድ የሚያወጣ ነው።

15 በአጠገብሽ የሚያልፉ ሁሉ፣እጃቸውን ያጨበጭቡብሻል፤“የውበት መደምደሚያ፣ የምድር ሁሉ ደስታ፣የተባለች ከተማ ይህች ናትን?”እያሉ ራሳቸውን በመነቅነቅ፣በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያሾፋሉ።

16 ጠላቶችሽ ሁሉ በአንድ ላይ፣አፋቸውን በኀይል ከፈቱ፤ጥርሳቸውን እያፏጩ አሾፉ፤እንዲህም አሉ፤ “ውጠናታል፤የናፈቅነው ጊዜ ይህ ነበር፤ኖረንም ልናየው በቃን።”