1 ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤
2 እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤ እግዚአብሔር የሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል
3 እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ በኀይሉም ታላቅ ነው፤ እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።
4 ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል።ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።
5 ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤ኰረብቶችም ቀለጡ።ምድር በፊቱ፣ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።
6 ቊጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል?ጽኑ ቊጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል?መዓቱ እንደ እሳት ፈሶአል፤ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።