19 ደናግሉ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰብስበው ሳለ፣ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ነበር።
20 አስቴር ግን ልክ መርዶክዮስ እንደ ነገራት የማን ወገንና የየት አገር ሰው እንደሆነች ደብቃ ነበር፤ ይህ የሆነበት ምክንያት መርዶክዮስ በሚያሳድጋት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ፣ አሁንም ምክሩን ትከተል ስለ ነበር ነው።
21 መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ሳለ፣ በሩን ከሚጠብቁት ከንጉሡ የጦር አለቆች ሁለቱ ገበታና ታራ ተቈጡ፤ ንጉሥ ጠረክሲስንም ለመግደል ዶለቱ።
22 መርዶክዮስም አድማውን ስለ ደረሰበት፣ ለንግሥት አስቴር ገለጠላት፤ እርሷም ይህን ከመርዶክዮስ ማግኘቷን ለንጉሡ ገልጣ ነገረችው።
23 ነገሩ ሲጣራም እውነት ሆኖ ተገኘ፤ ሁለቱም ሹማምት በስቅላት ሞት ተቀጡ። ይህ ሁሉ በንጉሡ ፊት በታሪክ መዝገብ ተጻፈ።