አስቴር 2:5-11 NASV

5 በዚህ ጊዜ ከብንያም ነገድ የቂስ ልጅ፣ የሰሜኢ ልጅ፣ የኢያዕር ልጅ መርዶክዮስ የሚባል አንድ አይሁዳዊ በሱሳ ግንብ ይኖር ነበር፤

6 እርሱም የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከይሁዳ ንጉሥ ከኢኮንያን ጋር ከኢየሩሳሌም በምርኮ ከተወሰዱት አንዱ ነበር።

7 መርዶክዮስ አንዲት ሀደሳ የምትባል የአጎቱ ልጅ ነበረችው፤ አባትና እናት ስላልነበራት፣ ያሳደጋት እርሱ ነበር። አስቴር ተብላ የምትጠራው ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች። አባቷና እናቷ ከሞቱ በኋላ መርዶክዮስ እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ወሰዳት።

8 የንጉሡ ትእዛዝና ዐዋጅ በወጣ ጊዜ፣ ብዙ ልጃገረዶች ወደ ሱሳ ግንብ ተወስደው ለጠባቂው ለሄጌ ተሰጡ፤ አስቴርም ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ተወስዳ፣ ለሴቶቹ ጠባቂ ለሄጌ በዐደራ ተሰጠች።

9 ልጃገረዲቱም ደስ አሰኘችው፤ በእርሱም ዘንድ መወደድን አተረፈች፤ እርሱም የውበት መንከባከቢያዋንና የተለየ ምግብ ወዲያውኑ ሰጣት። ከቤተ መንግሥቱ የተመረጡ ሰባት ደንገጡሮችን በመመደብም እርሷንና ደንገጡሮቿን ምርጥ ወደ ሆነው የሴቶች መጠበቂያ አዛወረ።

10 መርዶክዮስ እንዳትናገር አዞአት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደሆነች አልገለጸችም።

11 መርዶክዮስም አስቴር እንዴት እንደሆነችና ምንስ እንዳጋጠማት ለማወቅ፣ በየዕለቱ በሴቶች መጠበቂያ አደባባይ አጠገብ ወዲያና ወዲህ ይመላለስ ነበር።