አስቴር 7:5-10 NASV

5 ንጉሥ ጠረክሲስም ንግሥት አስቴርን፣ “ለመሆኑ እርሱ ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እስከዚህ የደፈረውስ ሰው የታለ?” ሲል ጠየቀ።

6 አስቴርም፣ “ያ ባላጋራና ጠላት ይህ ክፉው ሐማ ነው” አለች።ከዚያም ሐማ በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት እጅግ ደነገጠ።

7 ንጉሡ ከተቀመጠበት በቊጣ ተነሣ፤ የወይን ጠጁንም ትቶ ወደ ቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ሄደ። ሐማ ግን ንጉሡ ሊያጠፋው ቈርጦ መነሣቱን ስላወቀ፣ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን እንድታተርፍለት ለመማጠን በዚያው ቀረ።

8 ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ሲመለስ አስቴር ደገፍ ባለችበት ድንክ ዐልጋ ላይ ሐማ ተደፍቶ ነበር።ንጉሡም፣ “ይባስ ብሎ አብራኝ ያለችውን ንግሥት በገዛ ቤቴ ሊደፍራት ያስባልን?” ሲል ተናገረ።ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ ገና እንደ ወጣ፣ የሐማን ፊት ሸፈኑት።

9 ከዚያም ንጉሡን በቅርብ ከሚያገለግሉት ጃንደረቦች አንዱ የሆነው ሐርቦና፣ “እነሆ ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ በሐማ ቤት አጠገብ ተተክሎአል፤ ይህን ያዘጋጀው ንጉሡን ለማዳን በጎ ነገር ለተናገረው ለመርዶክዮስ ነው” አለ።ንጉሡም፣ “በዚሁ ላይ ስቀሉት” አለ።

10 ስለዚህ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሐማን ሰቀሉት፤ ከዚያም የንጉሡ ቊጣ በረደ።