አስቴር 8:5-11 NASV

5 እንዲህም አለች፤ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘውና እኔም በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጉዳዩም በንጉሡ ዘንድ ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔም ደስ ከተሰኘ፣ የአጋጋዊው የሐመዳቱ ልጅ ሐማ በንጉሡ አውራጃዎች ሁሉ የሚገኙትን አይሁድ ለማጥፋት የሸረበውን ሤራና የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ።

6 በሕዝቤ ላይ መዐት ሲወርድ እያየሁ እንዴት ልታገሥ እችላለሁ? የቤተ ሰቤንስ መጥፋት እያየሁ እንዴት መቋቋም እችላለሁ?”

7 ንጉሥ ጠረክሲስም ለንግሥት አስቴርና ለአይሁዳዊው ለመርዶክዮስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እነሆ ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ስላቀደ፣ ቤት ንብረቱን ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለውታል።

8 በንጉሥ ስም የተጻፈናበቀ ለበቱ የታተመ ደብዳቤ ሊሻር ስለማይችል፣ እናንተ ደግሞ አይሁድን በተመለከተ መልካም መስሎ የታያችሁን ሌላ ዐዋጅ በንጉሡ ስም ጽፋችሁ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም አትሙት።”

9 ኒሳን በተባለው በሦስተኛው ወር ሃያ ሦስተኛ ቀን የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊዎች በአስቸኳይ ተጠርተው ነበር፤ እነርሱም የመርዶክዮስን ትእዛዝ ሁሉ ለአይሁድ፣ እንዲሁም ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ፣ በአንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚገኙ እንደራሴዎች፣ የአውራጃ ገዦችና መኳንንት ሁሉ ጻፉ። እነዚህም ትእዛዞች የተጻፉት በእያንዳንዱ አውራጃ ፊደልና በእያንዳንዱ ሕዝብ ቋንቋ፣ እንደዚሁም ለአይሁድ በገዛ ፊደላቸውና በገዛ ቋንቋቸው ነበር።

10 መርዶክዮስ ትእዛዙን በንጉሥ ጠረክሲስ ስም ጽፎ በንጉሡ የቀለበት ማኅተም አተመው፤ ከዚያም በተለይ ለንጉሡ በተገሩ ፈጣን ፈረሶች በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው።

11 የንጉሡም ዐዋጅ በየከተማው የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ እንዲሰበሰቡና ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲሁም በራሳቸው፣ በሚስቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ አደጋ የሚያደርስባቸውን የየትኛውንም ዜጋ ወይም አውራጃ የታጠቀ ኀይል እንዲያጠፉ፣ እንዲገድሉ፣ እንዲደመስሱና የጠላቶቻቸውን ሀብት እንዲዘርፉ ፈቀደላቸው።