አስቴር 9:25-31 NASV

25 ሤራው በንጉሡ ዘንድ እንደ ታወቀ ሐማ በአይሁድ ላይ የሸረበው ሤራ በገዛ ራሱ ላይ እንዲጠመጠም፣ እርሱና ወንዶች ልጆቹም በዕንጨት ላይ እንዲሰቀሉ የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ።

26 ስለዚህ እነዚህ ቀኖች ፉር ከሚለው ቃል “ፉሪም” ለመባል በቁ። በዚህ ደብዳቤ ስለ ተጻፈው ሁሉ፣ ስላዩትና ስለ ደረሰባቸውም ነገር ሁሉ፣

27 አይሁድ በታዘዘውና በተወሰነው ጊዜ እነርሱና ዘሮቻቸው፣ እነርሱን የተጠጓቸውም ሁሉ እነዚህን ሁለት ቀኖች በየዓመቱ ባለማቋረጥ እንዲያከብሩ ሥርዐት አድርገው ራሳቸው ወሰኑ።

28 እነዚህም ቀኖች በእያንዳንዱ ትውልድ፣ በእያንዳንዱ ቤተ ሰብ፣ በእያንዳንዱ አውራጃና በእያንዳንዱ ከተማ መታሰብና መከበር ይኖርባቸዋል፤ ይኸውም እነዚህ የፉሪም ቀኖች በአይሁድ ዘንድ ሳይከበሩ እንዳይቀሩ፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል እንዳይደመሰስ ነው።

29 ስለዚህ የአቢካኢል ልጅ ንግሥት አስቴር ከአይሁዳዊው ከመርዶክዮስ ጋር በመሆን፣ ፉሪምን አስመልክተው ይህችን ሁለተኛዪቱን ደብዳቤ ለማጽናት በሙሉ ሥልጣን ጻፉ።

30 መርዶክዮስም የመልካም ምኞት መግለጫና ማረጋገጫ የሆነውን ደብዳቤ በጠረክሲስ ግዛት ውስጥ በሚገኙት አንድ መቶ ሃያ ሰባት አውራጃዎች ለሚኖሩት አይሁድ ሁሉ ላከ፤

31 የላከውም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባወጁላቸውና እንደዚሁም የጾሙንና የሰቈቃውን ጊዜ በሚመለከት ለራሳቸውና ለዘራቸው ባጸኑት ውሳኔ መሠረት እነዚህ የፉሪም ቀኖች በተወሰነላቸው ጊዜ እንዲከበሩ ነው።