3 ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤ልጆቻችሁ ለልጆቻቸው ይንገሩ፤ልጆቻቸውም ለሚቀጥለው ትውልድ ይንገሩ።
4 ከአንበጣ መንጋ የተረፈውን፣ትልልቁ አንበጣ በላው፤ከትልልቁ አንበጣ የተረፈውን፣ኵብኵባ በላው፤ከኵብኵባ የተረፈውን፣ሌሎች አንበጦች በሉት።
5 እናንት ሰካራሞች፤ ተነሡ፤ አልቅሱ፤እናንት የወይን ጠጅ ጠጪዎች ሁሉ፤ ዋይ በሉ፤ስለ አዲሱ የወይን ጠጅ ዋይ ብላችሁ አልቅሱ፤አፋችሁ ላይ እንዳለ ተነጥቃችኋልና።
6 ኀያልና ቊጥር ስፍር የሌለው ሕዝብ፣ምድሬን ወሮአታልና፤ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ፣መንጋጋውም እንደ እንስት አንበሳ መንጋጋ ነው።
7 የወይን ቦታዬን ባድማ አደረገው፤የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስኪታዩ ድረስ፣ቅርፊታቸውን ልጦ፣ወዲያ ጣላቸው።
8 የልጅነት እጮኛዋን እንዳጣች ድንግል፣ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ።
9 የእህል ቊርባንና የመጠጥ ቍርባን፣ ከእግዚአብሔር ቤት ተቋርጦአል፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚያገለግሉ፣ካህናት ያለቅሳሉ።