ኢዩኤል 2:17-23 NASV

17 በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግሉ ካህናት፣በመሠዊያውና በቤተ መቅደሱ አደባባይ መካከል ሆነው ያልቅሱ፤እንዲህም ይበሉ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህን አድን፤ርስትህን በአሕዛብ መካከል መተረቻ፣መሣቂያና መሣለቂያም አታድርግ፤ለምንስ በሕዝቦች መካከል፣‘አምላካቸው ወዴት ነው?’ ይበሉን።”

18 እነሆ፤ እግዚአብሔር ስለ ምድሩ ይቀናል፤ስለ ሕዝቡም ይራራል።

19 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል ይመልስላቸዋል፤“እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅና ዘይት፣እስክትጠግቡ ድረስ እሰጣችኋለሁ፤የሕዝቦች መዘባበቻ አላደርጋችሁም።

20 “የሰሜንን ሰራዊት ከእናንተ አርቃለሁ፤ፊቱን ወደ ምሥራቁ ባሕር፣ጀርባውንም ወደ ምዕራቡ ባሕር በማድረግ፣ወደ ደረቀውና ወደ ባድማው ምድር እገፋዋለሁ፤ግማቱ ይወጣል፤ክርፋቱም ይነሣል።”በእርግጥ እርሱ ታላቅ ነገር አድርጎአል።

21 ምድር ሆይ፤ አትፍሪ፤ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤በእርግጥ እግዚአብሔር ታላቅ ነገር አድርጎአል።

22 የዱር እንስሳት ሆይ፤ አትፍሩ፤መሰማሪያ መስኮቹ ለምልመዋልና፤ዛፎቹ ፍሬያቸውን አፍርተዋል፤የበለሱ ዛፍና የወይኑ ተክልም እጅግ አፍርተዋል።

23 የጽዮን ሰዎች ሆይ፤ ደስ ይበላችሁ፤በአምላካችሁ በእግዚአብሔር፣ ሐሤት አድርጉ፤የበልግን ዝናብ፣በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና፤እንደ ቀድሞውም፣የበልግንና የጸደይን ዝናብ በብዛት ልኮላችኋል።