3 አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም።
4 ዕዝራ፣ ነገሩ በእጅህ ነው፤ ተነሥ! እኛም እንደግፍሃለን፤ በርትተህም፤ አድርገው።”
5 ዕዝራም ተነሥቶ ዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ ሌዋውያንና እስራኤል ሁሉ የቀረበውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ አስማላቸው፤ እነርሱም ማሉ።
6 ከዚያም ዕዝራ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ክፍል ገባ፤ ምርኮኞቹ ታማኞች ሆነው ባለ መገኘታቸው ያለቅስ ነበር፤ በዚያም ምግብ አልቀመሰም፤ ውሃም አልጠጣም።
7 ከዚያም ምርኮኞቹ ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ፤
8 ዐዋጁም በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንም ሰው በሹማምቱና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፣ ራሱም ከምርኮኞቹ ጉባኤ እንዲወገድ የሚያዝ ነበር።
9 ስለዚህ በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ በዘጠነኛው ወር በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ስለ ወቅቱ ጒዳይና ስለ ከባዱ ዝናብ በመጨነቅ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀምጠው ነበር።