5 ዕዝራም ተነሥቶ ዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ ሌዋውያንና እስራኤል ሁሉ የቀረበውን ሐሳብ እንዲፈጽሙ አስማላቸው፤ እነርሱም ማሉ።
6 ከዚያም ዕዝራ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ክፍል ገባ፤ ምርኮኞቹ ታማኞች ሆነው ባለ መገኘታቸው ያለቅስ ነበር፤ በዚያም ምግብ አልቀመሰም፤ ውሃም አልጠጣም።
7 ከዚያም ምርኮኞቹ ሁሉ በኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ፤
8 ዐዋጁም በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ማንም ሰው በሹማምቱና በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፣ ራሱም ከምርኮኞቹ ጉባኤ እንዲወገድ የሚያዝ ነበር።
9 ስለዚህ በሦስት ቀን ውስጥ የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ፤ በዘጠነኛው ወር በሃያኛውም ቀን ሕዝቡ ሁሉ ስለ ወቅቱ ጒዳይና ስለ ከባዱ ዝናብ በመጨነቅ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀምጠው ነበር።
10 ከዚያም ካህኑ ዕዝራ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ታማኞች አልነበራችሁም፤ በእስራኤል በደል ላይ በደል በመጨመር ባዕዳን ሴቶችን አገባችሁ።
11 አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ ፈቃዱን ፈጽሙ፤ በዙሪያችሁ ካሉት አሕዛብና ከባዕዳን ሚስቶቻችሁ ተለዩ።”