4 ከዚያም ለእያንዳንዱ ቀን እንደታዘዘው፣ በሚያስፈልገው ቊጥር ልክ የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ የዳስ በዓልን በተጻፈው መሠረት አከበሩ።
5 ከዚያም በኋላ መደበኛውን የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የወር መባቻን መሥዋዕት፣ በተቀደሱት የእግዚአብሔር በዓላት የሚቀርበውን መሥዋዕትና በበጎ ፈቃድ ለእግዚአብሔር የሚሰጠውን መባ አቀረቡ።
6 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት ገና ያልተጣለ ቢሆንም፣ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
7 ከዚያም ለድንጋይ ጠራቢዎችና ለዐናጢዎች ገንዘብ ሰጡ፤ ከፋርስ ንጉሥ ከጢሮስ በተፈቀደው መሠረት የዝግባ ዛፎች ከሊባኖስ ወደ ኢዮጴ በባሕር እንዲያመጡላቸው፣ ለሲዶናና ለጢሮስ ሰዎችም ምግብ፣ መጠጥና ዘይት ሰጡ።
8 ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር፣ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ እንዲሁም የቀሩት ወንድሞቻቸው (ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሁሉ) ሃያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው ሌዋውያን የእግዚአብሔርን ቤት ሕንጻ ሥራ እንዲቈጣጠሩ ሾሟቸው፤ ሥራውንም ጀመሩ።
9 ኢያሱ፣ ወንዶች ልጆቹና ወንድሞቹ፣ የዮሖዳያ ዘሮች ቀድምኤልና ወንዶች ልጆቹ፣ የኤንሐዳድ ወንዶች ልጆች፣ ልጆቻቸውና ወንድሞቻቸው፣ ሌዋውያኑም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት የሚሠሩትን ሰዎች ለመቈጣጠር በአንድ ላይ ሆኑ።
10 ግንበኞቹ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ ካህናቱ ልብሰ ተክህኖአቸውን ለብሰውና መለከታቸውን ይዘው፣ ሌዋውያኑ የአሳፍ ልጆች ደግሞ ጸናጽል ይዘው፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መመሪያ መሠረት እግዚአብሔርን ለመወደስ ስፍራቸውን ያዙ።