ዕዝራ 5:5-11 NASV

5 የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ መሪዎች ላይ ነበረ፤ ነገሩ ወደ ዳርዮስ ደርሶ የጽሑፍ መልስ እስኪያገኙ ድረስ አልተከለከሉም።

6 በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይ፣ ተባባሪዎቻቸውና በኤፍራጥስ ማዶ የነበሩ ሹማምት ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

7 የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤ለንጉሥ ዳርዮስ፣የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8 የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9 እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው።

10 የመሪዎቻቸውን ስም በጽሑፍ እናሳውቅህ ዘንድ ስማቸውን ደግሞ ጠየቅን።

11 የሰጡን መልስ ይህ ነው፤“እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁንም እንደ ገና የምንሠራው ቤተ መቅደስ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የጨረሰውን ነው።