ዕዝራ 5:7-13 NASV

7 የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤ለንጉሥ ዳርዮስ፣የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8 የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9 እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው።

10 የመሪዎቻቸውን ስም በጽሑፍ እናሳውቅህ ዘንድ ስማቸውን ደግሞ ጠየቅን።

11 የሰጡን መልስ ይህ ነው፤“እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁንም እንደ ገና የምንሠራው ቤተ መቅደስ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የጨረሰውን ነው።

12 ነገር ግን አባቶቻችን የሰማይን አምላክ አስቈጥተውት ስለ ነበር፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለከለዳዊው ናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤተ መቅደስ አፈራርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13 “ይሁንና ቂሮስ፣ የባቢሎን ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና እንዲሠሩ ንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ ሰጠ።