ዕዝራ 7:14-20 NASV

14 በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል።

15 ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤

16 እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ።

17 በዚህም ገንዘብ ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን፣ ከእህል ቊርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቊርባኖቻቸው ጋር መግዛት እንዳለብህ አትርሳ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ አቅርብ።

18 ከዚህ የሚቀረውንም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ አይሁድ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ደስ ለሚላችሁ ነገር ሁሉ አውሉት።

19 ለአምላክህ ቤተ መቅደስ በዐደራ የተሰጠህንም ዕቃ ሁሉ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ።

20 ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።