ዕዝራ 8:21-27 NASV

21 ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጒዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ።

22 “መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቊጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር።

23 ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24 እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤

25 ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው።

26 ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣

27 አንድ ሺህ ዳሪክ የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው።