ዘካርያስ 5:1-7 NASV

1 እንደ ገናም ተመለከትሁ፤ በዚያም በፊቴ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አየሁ።

2 እርሱም፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ጠየቀኝ። እኔም፣ “ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ዐሥር ክንድ የሆነ በራሪ የመጽሐፍ ጥቅልል አያለሁ” አልሁት።

3 እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ይህ በምድር ሁሉ ላይ የሚወጣ ርግማን ነው፤ በአንደኛው በኩል እንደ ተጻፈው የሚሰርቅ ሁሉ ይጠፋል፤ በሌላው በኩል ደግሞ እንደ ተጻፈው በሐሰት የሚምል ሁሉ ይጠፋልና።

4 እግዚአብሔር ጸባኦት ‘እኔ ርግማኑን አመጣዋለሁ፤ እርሱም ወደ ሌባው ቤትና በስሜ በሐሰት ወደሚምለው ሰው ቤት ይገባል፤ በዚያም ይቀመጣል፤ ቤቱን፣ እንጨቱንና ድንጋዩን ያጠፋል ይላል።”

5 ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወደ እኔ መጥቶ፣ “ወደ ላይ ተመልከት፤ ይህ የሚመጣው ምን እንደሆነ እይ” አለኝ።

6 እኔም፣ “ምንድን ነው?” አልሁት። እርሱም፣ “የኢፍ መስፈሪያ ነው” አለኝ። ቀጥሎም “ይህ በምድሪቱ ሁሉ ላይ ያለው የሕዝቡ በደል ነው” አለኝ።

7 ከዚያም ከእርሳስ የተሠራው ክዳን ተነሣ፤ የኢፍ መስፈሪያ ውስጥ አንዲት ሴት ተቀምጣ ነበር።