ዘካርያስ 3 NASV

ለሊቀ ካህኑ የሚሆን ንጹሕ ልብስ

1 እርሱም ሊቀ ካህኑን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ፣ ሰይጣንም ሊከሰው በስተ ቀኙ ቆሞ አሳየኝ።

2 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አንተ ሰይጣን፤ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ይህ ሰው ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው።

3 ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር።

4 መልአኩም ከፊቱ ቆመው የነበሩትን፣ “ያደፉ ልብሶቹን አውልቁለት” አላቸው።ኢያሱንም፣ “እነሆ፤ ኀጢአትህን ከአንተ አስወግጃለሁ፤ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ” አለው።

5 እኔም፣ “ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉለት” አልሁ። የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ እያለ፣ ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አደረጉለት፤ ልብስም አለበሱት።

6 የእግዚአብሔርም መልአክ ለኢያሱ ይህን ማስጠንቀቂያ ሰጠው፤

7 “እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በመንገዴ ብትሄድ፣ ትእዛዜንም ብትጠብቅ፣ ቤቴን ታስተዳድራለህ፤ በአደባባዮቼም ላይ ኀላፊ ትሆናለህ፤ በዚህ በቆሙት መካከል ቦታ እሰጥሃለሁ።

8 “ ‘ሊቀ ካህኑ ኢያሱ ሆይ፤ ስማ፤ በፊትህ የሚቀመጡትም ረዳቶችህ ገና ወደ ፊት ለሚመጡት ምልክት የሚሆኑ ሰዎች ናቸውና ይስሙ፤ እነሆ፤ ባሪያዬን ቊጥቋጡን አመጣለሁ።

9 በኢያሱ ፊት ያስቀመጥሁት ድንጋይ እነሆ! በዚያ በአንዱ ድንጋይ ላይ ሰባት ዐይኖች አሉ፤ በእርሱም ላይ ቅርጽ እቀርጻለሁ፤ የዚህችንም ምድር በደል በአንድ ቀን አስወግዳለሁ፤’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

10 “ ‘በዚያን ቀን እያንዳንዱ በገዛ ወይኑና በለሱ ሥር ሆኖ ባልንጀራውን ይጋብዛል፤’ ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14