1 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት በስምንተኛው ወር የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
2 “እግዚአብሔር በአባቶቻችሁ ላይ እጅግ ተቈጥቶ ነበር፤
3 ስለዚህ ለሕዝቡ ንገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ እኔ ተመለሱ’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ “እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤’ ይላል፤ እግዚአብሔር ጸባኦት፤
4 የቀደሙት ነቢያት፣ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት፣ “ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ’ ይላል በማለት ለአባቶቻችሁ ሰብከው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙም፤ እኔንም አላደመጡም፤ እንደ እነርሱ አትሁኑ፤ ይላል እግዚአብሔር።
5 አባቶቻችሁ አሁን የት አሉ? ነቢያትስ ለዘላለም በሕይወት ይኖራሉን?
6 ለባሪያዎቼ ለነቢያት ያዘዝኋቸው ቃልና ሥርዐት በአባቶቻችሁ ላይ አልደረሰምን?“እነርሱም ንስሓ ገብተው፤ እንዲህ አሉ፤ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት በወሰነው መሠረት፣ ለሥራችንና ለመንገዳችን የሚገባውን አድርጎብናል።’ ”
7 ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ ሳባጥ በሚባለው በዐሥራ አንደኛው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ የእግዚአብሔር ቃል ወደ አዶ ልጅ ወደ በራክዩ ልጅ ወደ ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤
8 በምሽት ራእይ አየሁ፤ እዚያም በፊቴ አንድ ሰው በመጋላ ፈረስ ላይ ተቀምጦአል፤ እርሱም በሸለቆ ውስጥ በባርሰነት ዛፎች መካከልም ቆሞ ነበር፤ ከበስተ ኋላውም መጋላ፣ ሐመርና አንባላይ ፈረሶች ነበሩ።
9 እኔም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁ።ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክም፣ “እነዚህ ምን እንደሆኑ አሳይሃለሁ” አለኝ።
10 ከዚያም በባርሰነት ዛፎች መካከል የቆመው ሰው፣ “እነዚህ በምድር ሁሉ እንዲመላለሱ እግዚአብሔር የላካቸው ናቸው” ሲል መለሰ።
11 እነርሱም በባርሰነት ዛፎች መካከል ቆሞ ለነበረው የእግዚአብሔር መልአክ፣ “በምድር ሁሉ ተመላለስን፤ መላዋ ምድርም ዐርፋ በሰላም ተቀምጣለች” ብለው መለሱለት።
12 ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ፣ “እግዚአብሔር ጸባኦት ሆይ፤ በእነዚህ ሰባ ዓመታት ውስጥ የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” አለ።
13 እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ ደስ በሚያሰኝና በሚያጽናና ቃል መለሰለት።
14 ከዚያም ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ተናገር፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ጽዮንና ስለ ኢየሩሳሌም እጅግ ቀንቻለሁ፤
15 ሰላም አለ በሚሉ አሕዛብ ላይ ግን በጣም ተቈጥቻለሁ፤ በመጠኑ ተቈጥቼ ሳለሁ፣ እነርሱ ግን ጥፋቱ እንዲብስ አደረጉ።’
16 “ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በምሕረት ወደ ኢየሩሳሌም እመለሳለሁ፤ በዚያም ቤቴ እንደ ገና ይሠራል፤ መለኪያ ገመድም በኢየሩሳሌም ላይ ይዘረጋል’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።’
17 “ቀጥለህም እንዲህ እያልህ ስበክ፤ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ከተሞቼ እንደ ገና ብልጽግና ይትረፈረፍባቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ገና ጽዮንን ያጽናናል፤ ኢየሩሳሌምንም ይመርጣል።’ ”
18 ከዚያም ወደ ላይ ተመለከትሁ፤ ከፊቴም አራት ቀንዶችን አየሁ፤
19 ከእኔ ጋር ይነጋገር የነበረውንም መልአክ፣ “እነዚህ ምንድን ናቸው?” አልሁት።እርሱም፣ “እነዚህ ይሁዳን፣ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን የበታተኑ ቀንዶች ናቸው” አለኝ።
20 ከዚያም እግዚአብሔር አራት የእጅ ሙያተኞችን አሳየኝ።
21 እኔም፣ “እነዚህስ ምን ሊያደርጉ መጡ?” አልሁ።እርሱም፣ “እነዚህ ቀንዶች ማንም ራሱን ቀና ማድረግ እንዳይችል ይሁዳን የበታተኑ ናቸው፤ እነዚህ የእጅ ሙያተኞች ግን የመጡት እነርሱን ሊያስደነግጧቸው፣ ሕዝቡን ለመበታተን በይሁዳ ምድር ላይ ቀንዳቸውን ያነሡትን የእነዚህን የአሕዛብ ቀንዶች ሰብሮ ለመጣል ነው” አለኝ።