ዘካርያስ 13 NASV

ከኀጢአት መንጻት

1 “በዚያ ቀን የዳዊትን ቤትና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች ከኀጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።

2 “በዚያ ቀን የጣዖታትን ስም ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ ከእንግዲህም አይታሰቡም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። “ነቢያትንና ርኵስ መንፈስን ከምድሪቱ አስወግዳለሁ።

3 ማንም ትንቢት ቢናገር ወላጅ አባትና እናቱ፣ ‘በእግዚአብሔር ስም ሐሰት ተናግረሃልና ሞት ይገባሃል’ ይሉታል። ትንቢት ሲናገርም የገዛ ወላጆቹ ይወጉታል።

4 “በዚያን ቀን እያንዳንዱ ነቢይ ስለሚናገረው የትንቢት ራእይ ያፍራል፤ ለማታለልም የነቢያትን ጠጒራም ልብስ አይለብስም።

5 እርሱም፣ ‘እኔ ገበሬ እንጂ ነቢይ አይደለሁም፤ ከልጅነቴ ጀምሮ ኑሮዬ የተመሠረተውም በዕርሻ ላይ ነው’ ይላል።

6 አንድ ሰው፣ ‘ይህ በሰውነትህ ላይ ያለው ቊስል ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቀው፣ ‘በባልንጀሮቼ ቤት ሳለሁ የቈሰልሁት ነው’ ይላል።

እረኛው ተመታ፤ በጎቹ ተበተኑ

7 እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤“ሰይፍ ሆይ፤ በእረኛዬ፣በቅርብ ወዳጄ ላይ ንቃ!እረኛውን ምታ፤በጎቹ ይበተናሉ፤እኔም ክንዴን ወደ ታናናሾቹ አዞራለሁ።

8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የምድር ሁሉ፣ሁለት ሦስተኛው ተመትቶ ይጠፋል፤አንድ ሦስተኛው ግን በውስጡ ይቀራል፤

9 ይህን አንድ ሦስተኛውን ክፍል ወደ እሳት አመጣለሁ፤እንደ ብር አነጥራቸዋለሁ፤እንደ ወርቅም እፈትናቸዋለሁ፤እነርሱ ስሜን ይጠራሉ፤እኔም እመልስላቸዋለሁ፤እኔም፣ ‘ሕዝቤ ናቸው’ እላለሁ፤እነርሱም፣ ‘እግዚአብሔር አምላካችን ነው’ ይላሉ።”

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14