ዘዳግም 1:25-31 NASV

25 ከምድሪቱም ፍሬ ወደ እኛ ይዘው በመምጣት፣ “አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጠን ምድር መልካም ናት” ብለው ነገሩን።

26 እናንተ ግን ለመውጣት ፈቃደኞች አልነበራችሁም፤ በአምላካችን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ።

27 በየድንኳኖቻችሁ ሆናችሁ እንዲህ ስትሉ አጒረመረማችሁ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ጠልቶናል፤ ስለዚህም ከግብፅ ያወጣን አሞራውያን እንዲያጠፉን፣ በእጃቸው አሳልፎ ሊሰጠን ነው።

28 ታዲያ ወዴት መሄድ እንችላለን? ወንድሞቻችን፣ ‘ሰዎቹ ከእኛ ይልቅ ብርቱዎችና ቁመተ ረጃጅሞች፣ ከተሞቹም ትልልቆችና እስከ ሰማይ በሚደርስ ቅጥር የታጠሩ ናቸው፤ እንዲያውም በዚያ የዔናቅን ልጆች አይተናቸዋል’ ሲሉ እንድንፈራ አድርገውናል።”

29 እኔም አልኋችሁ፤ “አትሸበሩ፤ አትፍሯቸውም።

30 በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚህ በፊት ዐይናችሁ እያየ በግብፅ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፣ አሁንም ለእናንተ ይዋጋል፤

31 በምድረ በዳው እንደ አደረገው ሁሉ። በዚያም አባት ልጁን እንደሚሸከም፣ እናንተን አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እዚህ ስፍራ እስክትደርሱ በመጣችሁበት መንገድ ሁሉ እንዴት እንደ ተሸከማችሁ አይታችኋል።”