ዘዳግም 28 NASV

በመታዘዝ የሚገኝ በረከት

1 ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል።

2 አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም።

3 በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ።

4 የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ።

5 እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካሉ።

6 ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ።

7 እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ።

8 እግዚአብሔር (ያህዌ) በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል።

9 የአምላክህን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤

10 ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም።

11 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል።

12 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም።

13 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ መቼውንም ቢሆን እላይ እንጂ ፈጽሞ እታች አትሆንም።

14 ሌሎችን አማልክት በመከተል እነርሱን በማገልገል ዛሬ ከምሰጥህ ትእዛዞች ቀኝም ግራም አትበል።

አለመታዘዝ የሚያስከትላቸው ርግማኖች

15 ነገር ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባትታዘዝ በዛሬዋ ዕለት የምሰጥህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን ሁሉ በጥንቃቄ ባትከተላቸው፣ እነዚህ ርግማኖች ሁሉ ይደርሱብሃል፤ ያጥለቀ ልቁሃልም፦

16 በከተማ ትረገማለህ፤ በዕርሻም ትረገማለህ።

17 እንቅብህና ቡሓቃህ የተረገሙ ይሆናሉ።

18 የማሕፀንህ ፍሬ፣ የዕርሻህ ሰብል፣ የመንጋህ ጥጆች፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህ ይረገማሉ።

19 ስትገባ ትረገማለህ፤ ስትወጣም ትረገማለህ።

20 እርሱን በመተው ክፉ ድርጊት ከመፈጸምህ የተነሣ፣ እስክትደመሰስ ፈጥነህም እስክትጠፋ ድረስ እጅህ በነካው ሁሉ ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ርግማንን፣ መደናገርንና ተግሣጽን ይሰድብሃል።

21 እግዚአብሔር (ያህዌ) ልትወርሳት ከምትገባባት ምድር ላይ እስኪ ያጠፋህ ድረስም፣ በደዌ ይቀሥፍሃል።

22 እግዚአብሔር (ያህዌ) እስክትጠፋ ድረስ በሚቀሥፍ ደዌ፣ ትኵሳትና ዕባጭ፣ ኀይለኛ ሙቀትና ድርቅ፣ ዋግና አረማሞ ይመታሃል።

23 ከራስህ በላይ ያለው ሰማይ ናስ፣ ከእግርህ በታች ያለው ምድርም ብረት ይሆናል።

24 እግዚአብሔር (ያህዌ) የምድርህን ዝናብ ወደ ዐቧራነትና ወደ ትቢያነት ይለውጠዋል፤ ይህም እስክትጠፋ ድረስ ከሰማይ ይወርድብሃል።

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) በጠላቶችህ ፊት እንድትሸነፍ ያደርግሃል፤ በአንድ አቅጣጫ ትመጣባቸዋለህ፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫ ከፊታቸው ትሸሻለህ፤ ለምድር መንግሥታትም ሁሉ መሸማቀቂያ ትሆናለህ።

26 ሬሳህ የሰማይ አሞሮችና የምድር አራዊት ሲሳይ ይሆናል፤ በማስፈራራትም የሚያባርራቸው አይኖርም።

27 እግዚአብሔር (ያህዌ) በማትድንበት በግብፅ ብጉንጅ፣ በእባጭ፣ በሚመግል ቊስልና በዕከክ ያሠቃይሃል።

28 እግዚአብሔር (ያህዌ) በእብደት በዕውርነትና ግራ በማጋባት ያስጨንቅሃል።

29 በእኩለ ቀን፣ በጨለማ እንዳለ ዕውር በዳበሳ ትሄዳለህ። የምታደርገው ሁሉ አይሳካልህም። በየዕለቱ ትጨቈናለህ፤ ትመዘበራለህም፤ የሚታደግህ አይኖርም።

30 ሚስት ለማግባት ልጃገረድ ታጫለህ፤ ሌላው ግን ወስዶ ይደፍራታል። ቤት ትሠራለህ፣ ግን አትኖርበትም። ወይን ትተክላለህ፤ ፍሬውን ግን አትበላም።

31 በሬህ ዐይንህ እያየ ይታረዳል፤ ከሥጋውም አንዳች አትቀምስም። አህያህም በግድ ይወሰድብሃል፤ አይመለስልህም። በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚያስጥላቸውም አይኖርም።

32 ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለባዕድ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ እጅህንም ለማንሣት ዐቅም ታጣለህ፤ ከዛሬ ነገ ይመጣሉ፤ በማለትም ዐይኖችህ ሁል ጊዜ እነርሱን በመጠባበቅ ይደክማሉ።

33 የምድርህንና የድካምህን ፍሬ ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ ዕድሜ ልክህን በጭካኔና በጭቈና ከመኖር በቀር የሚተርፍህ ነገር አይኖርም።

34 የምታየው ሁሉ ያሳብድሃል።

35 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእግርህ ጥፍር እስከ ራስህ ጠጒር በሚዛመት፣ ሊድን በማይችልና በሚያሠቃይ ቊስል ጒልበትህንና እግርህን ይመታሃል።

36 እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንና በላይህ ያነገሥኸውን ንጉሥ፣ አንተና አባቶችህ ወደማታውቁት ሕዝብ ይወስዳችኋል፤ ከዚያም ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ።

37 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንድትገባ በሚያደርግበት ምድር ለአሕዛብ ሁሉ መሸማቀቂያ፣ ማላገጫና መዘባበቻ ትሆናለህ።

38 በዕርሻ ላይ ብዙ ዘር ትዘራለህ፤ አንበጣ ስለሚበላው የምትሰበስበው ጥቂት ይሆናል።

39 ወይን ትተክላለህ፤ ትንከባከበዋለህ፤ ነገር ግን ዘለላውን አትሰበስብም።

40 በአገርህ ምድር ሁሉ የወይራ ዛፍ ይኖርሃል፤ ፍሬው ስለሚረግፍብህ ግን ዘይቱን አትጠቀምበትም።

41 ወንዶችና ሴቶች ልጆች ትወልዳለህ፤ ነገር ግን በምርኮ ስለሚወሰዱ፣ አብረውህ አይኖሩም።

42 ዛፍህንና የምድርህን ሰብል ሁሉ የአንበጣ መንጋ ይወረዋል።

43 በመካከልህ የሚኖር መጻተኛ ከአንተ በላይ ከፍ ከፍ ሲል አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ።

44 እርሱ ያበድርሃል እንጂ አንተ አታበድረውም። እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተ ግን ጅራት ትሆናለህ።

45 እነዚህ ርግማኖች ሁሉ በአንተ ላይ ይመጣሉ፤ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስላል ታዘዝህና የሰጠህን ትእዛዝና ሥርዐት ስላልጠበቅህ እስክትጠፋ ድረስ ይከተሉሃል፤ ይወርዱብሃልም።

46 ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም ምልክትና መገረም ይሆናሉ።

47 በብልጽግና ጊዜ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በደስታና በሐሤት ስላላገለገልኸው፣

48 በራብና በጥም፣ በእርዛትና በከፋ ድኽነት እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስነሣብህን ጠላቶችህን ታገለግላለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በዐንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭንብሃል።

49 እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ንስር ፈጥኖ የሚወርድንና ቋንቋውን የማታውቀውን ሕዝብ እጅግ ሩቅ ከሆነ፣ ከምድርም ዳርቻ ያሰነሣብሃል፤

50 ሽማግሌ የማያከብር፣ ለብላቴና የማይራራ፣ ሲያዩት የሚያስፈራ ሕዝብ ነው።

51 እስክትጠፋም ድረስ የእንስሳትህን ግልገልና የምድርህን ሰብል ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህል፣ አዲስ የወይን ጠጅ ሆነ ዘይት፣ የመንጋህን ጥጃ ሆነ፣ የበግና ፍየል መንጋህን ግልገል አያስቀርልህም።

52 የምትታመንባቸውን ታላላቅ የተመሸጉ ቅጥሮች እስኪወድቁ ድረስ በመላው አገርህ ያሉትን ከተሞችህን ሁሉ ይከባል፤ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ምድር ያሉትን ከተሞች በሙሉ ይወራቸዋል።

53 ጠላቶችህ ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ ከሥቃይ የተነሣ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሰጠህን፣ የወገብህ ፍሬ የሆኑትን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ።

54 ሌላው ይቅርና በመካከልህ በጣም ደግና ርኅሩኅ የሆነው ሰው እንኳ ለገዛ ወንድሙ ወይም ለሚወዳት ሚስቱ ወይም ለተረፉት ልጆቹ አይራራላቸውም።

55 ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ላይም ቅንጣት ታህል እንኳ ከእነርሱ ለአንዱ አያቀምስም፤ ከተሞችህ ሁሉ በመከበባቸው ጠላቶችህ ከሚያደርሱብህ ሥቃይ የተነሣ ለእርሱ የቀረለት ይህ ብቻ ነውና።

56 በመካከልህ ተለሳልሳና ተቀማጥላ የምትኖር፣ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ፣ እግሯን ዐፈር ነክቶት የማያውቅ ሴት፣ የምትወደውን ባሏን፣ የገዛ ወንድ ወይም ሴት ልጆቿን ትንቃለች።

57 ከማሕፀኗ የወጣውን እንግዴ ልጇንና የምትወልዳቸውን ሕፃናት ትጠየፋለች፤ ይህን የምታደርገውም በመከራው ወቅት ጠላቶችህ ከተሞችህን ከበው በሚያስጨንቁህ ጊዜ፣ እነርሱን ደብቃ ለመብላት ስትል ነው።

58 በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የዚህን ሕግ ቃሎች በጥንቃቄ ባትከተልና አስደናቂና አስፈሪ የሆነውን የአምላክህንየእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ስም ባታከብር፣

59 እግዚአብሔር (ያህዌ) አስፈሪ መቅሠፍት፣ አስጨናቂና ለብዙ ጊዜ የሚቈይ መዓት፣ አሠቃቂና በቀላሉ የማይወገድ ደዌ በአንተና በዘሮችህ ላይ ይልክባችኋል።

60 የምትፈራቸውንም የግብፅ በሽታዎች ሁሉ ያመጣብሃል፤ በአንተም ላይ ይጣበቃሉ።

61 ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ የሕግ መጽሐፍ ያልተጻፈውን ማንኛውንም ዐይነት ደዌና መከራ እስክትጠፋ ድረስ ያመጣብሃል።

62 ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስላልታዘዛችሁ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት በዝታችሁ የነበራችሁት እናንተ ጥቂት ብቻ ትቀራላችሁ።

63 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በማበልጸግና ቊጥራችሁን በማብዛት ደስ እንደ ተሰኘ፣ እናንተን በማጥፋትና በመደምሰስም ደስ ይለዋል፤ ልትወርሷት ከምትገቡባት ምድር ትነቀላላችሁ።

64 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአንዱ የምድር ዳርቻ እስከ ሌላው ዳርቻ በሕዝቦች ሁሉ መካከል ይበትንሃል። በዚያ አንተም ሆንህ አባቶችህ የማታውቋቸውን ከዕንጨትና ከድንጋይ የተሠሩ ሌሎች አማልክትን ታመልካለህ።

65 በእነዚያ ሕዝቦች መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ ቦታ አይኖርም። እዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚጨነቅ አእምሮ፣ በናፍቆት የሚደክም ዐይንና ተስፋ የሚቈርጥ ልብ ይሰጥሃል።

66 ቀንም ሆነ ሌሊት በፍርሀት እንደ ተዋጥህ፣ ሕይወትህ ዋስትና ሳታገኝ፣ ዘወትር በሥጋት ትኖራለህ።

67 ልብህ በፍርሀት ከመሞላቱና ዐይንህ ከሚያየው የተነሣ፣ ሲነጋ፣ “ምነው አሁን በመሺ” ሲመሽ ደግሞ፣ “ምነው አሁን በነጋ!” ትላለህ።

68 ዳግመኛ አትመለስባትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር (ያህዌ) በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል። እዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሮች እንድትሆኗቸው ለጠላቶቻችሁ ለመሸጥ ራሳችሁን ታቀርባላችሁ፤ የሚገዛችሁ ግን አይኖርም።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34