ዘዳግም

ምዕራፎች 32

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1ሰማያት ሆይ፤ አድምጡ፤ እኔም እናገራለሁ፤ምድር ሆይ፤ አንቺም የአፌን ቃል ስሚ። 2ትምህርቴ እንደ ዝናብ ትውረድ፤ቃሌም እንደ ጤዛ ይንጠባጠብ፤በቡቃያ ሣር ላይ እንደ ካፊያ፣ለጋ ተክልም ላይ እንደ ከባድ ዝናብ ይውረድ። 3እኔ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ዐውጃለሁ፤የአምላካችንን (ኤሎሂም) ታላቅነት አወድሱ! 4እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም (ኤሎሂም) እርሱ ነው። 5በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም፤ወልጋዳና ጠማማ ትውልዶች ናቸው። 6አንተ ተላላና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣ ለእግዚአብሔር (ለያህዌ) የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን?አባትህ ፈጣሪህ፣የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን? 7የጥንቱን ዘመን አስታውስ፤አባትህን ጠይቅ፤ ይነግርሃልም፤ሽማግሌዎችህንም ጠይቅ፤ ያስረዱሃል። 8ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣በእስራኤል ልጆች ቊጥር ልክ፣የአሕዛብን ርስት ድንበር ለየ፤ 9 የእግዚአብሔር (ያህዌ) ድርሻ የገዛ ሕዝቡ፣ያዕቆብ የተለየ ርስቱ ነውና። 10እርሱን በምድረ በዳ፣ባዶና ጭው ባለ በረሓ ውስጥ አገኘው፤ጋሻ ሆነው፤ ተጠነቀቀለትም፤እንደ ዐይኑ ብሌን ጠበቀው። 11ንስር ጎጆዋን በትና፣በጫጩቶቿም ላይ እንደምትረብብ፣እነርሱን ለመያዝ ክንፎቿን እንደምትዘረጋ፣በክንፎቿም እንደምትሸከማቸው፣ 12 እግዚአብሔር (ያህዌ) ብቻ መራው፤ምንም ባዕድ አምላክ አብሮት አልነበረም። 13በምድር ከፍታ ላይ አወጣው፤የዕርሻንም ፍሬ መገበው፤ከዐለት ድንጋይ ማር አበላው፤ከባልጩትም ድንጋይ ዘይት መገበው። 14የላሙንና የበጉን መንጋ ቅቤና ወተት፣የሰቡትን በጎችና ፍየሎች፣የባሳንን ምርጥ አውራ በግ፣መልካም የሆነውንም ስንዴ፣ማለፊያውንም የወይን ጠጅ፣ 15ይሹሩን ወፈረ፤ ረገጠ፤ጠገበ፤ ሰውነቱ ደነደነ፤ ለሰለሰ፤የፈጠረውንም አምላክ (ኤሎሂም) ተወ፤መጠጊያ ዐለት የሆነውን አዳኙንም ናቀ። 16በባዕዳን አማልክታቸው አስቀኑት፤በአስጸያፊ ጣዖቶቻቸውም አስቈጡት። 17አምላክ ላልሆኑ አጋንንት፦ላላወቋቸው አማልክት፣ከጊዜ በኋላ ለተነሡ አማልክት፣አባቶቻችሁ ላልፈሯቸው አማልክት ሠዉ። 18አባት የሆነህን ዐለት ከዳኸው፤የወለደህን አምላክ (ኤሎሂም) ረሳኸው። 19 እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን አይቶ ናቃቸው፤በወንድና በሴት ልጆቹ ተቈጥቶአልና። 20እርሱም፣ “ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤”“መጨረሻቸው ምን እንደሚሆንም አያለሁ አለ፤ጠማማ ትውልድ፣የማይታመኑም ልጆች ናቸውና። 21አምላክ ባልሆነው አስቀኑኝ፤በከንቱ ጣዖቶቻቸው አስቈጡኝ።እኔም ሕዝብ ባልሆነው አስቀናቸዋለሁ።በማያስተውልም ሕዝብ አስቈጣቸዋለሁ። 22በቊጣዬ እሳት ተቀጣጥሎአልና፤እርሱ እስከ ሲኦል ዘልቆ ይነዳል።ምድርን እስከ ሰብሏ ይበላል፤የተራሮችንም መሠረት ያቀጣጥላል። 23“በመዓት ላይ መዓት አመጣባቸዋለሁ።ፍላጻዬንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ። 24የሚያጠፋ ራብ፣ በልቶ የሚጨርስ ቸነፈርና ከባድመቅሠፍት እሰድባቸዋለሁ፤የአራዊትን ሹል ጥርስ፣ በምድር የሚሳብ የእባብ መርዝምእሰድባቸዋለሁ። 25ሰይፍ መንገድ ላይ ያስቀራቸዋል፤ቤታቸውም ውስጥ ድንጋጤ ይነግሣል፤ጐልማሳውና ልጃገረዷ፣ሕፃኑና ሽማግሌው ይጠፋሉ። 26እበትናቸዋለሁ፤ ከሰዎችም መካከል መታሰቢያቸውንአጠፋለሁ አልሁ፤ 27ነገር ግን ጠላቶቻቸው እንዳይታበዩ፣‘ድል ያደረገችው እጃችን እንጂ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ይህን ሁሉ አላደረገም እንዳይሉ፣’ ”የጠላትን መነሣሣት ሠጋሁ። 28አእምሮ የጐደላቸው፣ማስተዋልም የሌላቸው ናቸው። 29አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር። 30መጠጊያ ዐለታቸው ካልሸጣቸው፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ካልተዋቸው በቀር፣አንድ ሰው እንዴት ሺሁን ያሳድዳል?ሁለቱስ እንዴት ዐሥር ሺሁን እንዲሸሹ ያደርጋሉ? 31የእነርሱ መጠጊያ ዐለት እንደ እኛ መጠጊያዐለት አይደለምና፤ ጠላቶቻችንም እንኳ ይህን አይክዱም። 32ወይናቸው ከሰዶም ወይን፣ከገሞራም እርሻ ይመጣል፤የወይናቸው ፍሬ በመርዝ፣ዘለላቸውም በምሬት የተሞላ ነው። 33ወይናቸው የእባብ መርዝ፣የመራዥ እባብም መርዝ ነው። 34“ይህ በእኔ ዘንድ ተጠብቆ ያለ፣በመዝገቤስ የታተመ አይደለምን? 35በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ፤ጊዜው ሲደርስ እግራቸው ይሰናከላል፤የመጥፊያቸው ቀን ቀርቦአል፤የሚመጣባቸውም ፍርድ ፈጥኖባቸዋል።” 36ኀይላቸው መድከሙን፣ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው አለመቅረቱን በሚያይበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሕዝቡ ይፈርዳል፤ለአገልጋዮቹም ይራራል። 37እንዲህም ይላል፤ “መጠጊያ ዐለት የሆኗቸው፣እነዚያ አማልክታቸው የት አሉ? 38የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፣የመጠጥ ቊርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ አማልክት ወዴት ናቸው?እስቲ ይነሡና ይርዷችሁ!እስቲ መጠለያ ይስጧችሁ! 39“እኔ ራሴ እርሱ እንደሆንሁ እዩ፤ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ የለም፤እገድላለሁ፤ አድናለሁም፤አቈስላለሁ፤ እፈውሳለሁም፤ከእጄም የሚያስጥል ማንም የለም። 40እጄን ወደ ሰማይ አነሣለሁ፤ለዘላለምም ሕያው እንደሆንሁ እናገራለሁ፤ 41የሚያብረቀርቅ ሰይፌን ስዬ፣እጄ ለፍርድ ስትይዘው፣ባላጋራዎቼን እበቀላቸዋለሁ፤የሚጠሉኝንም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ። 42ሰይፌ ሥጋ በሚበላበት ጊዜ፣ፍላጾቼ በደም እንዲሰክሩ አደርጋለሁ፤ደሙ የታረዱትና የምርኮኞች፣የጠላት አለቆችም ራስ ደም ነው።” 43አሕዛብ ሆይ፤ ከሕዝቡ ጋር ደስ ይበላችሁ፤እርሱ የአገልጋዮቹን ደም ይመልሳል፤ጠላቶቹንም ይበቀላል።ምድሪቱንና ሕዝቡን ይቤዣቸዋልና። 44ሙሴም ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ጋር መጥቶ የዚህን መዝሙር ቃሎች በሕዝቡ ጆሮ ተናገረ። 45ሙሴም እነዚህን ቃሎች ሁሉ ለመላው እስራኤል ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ 46እንዲህ አላቸው፤ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በጥንቃቄ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዟቸው፣ እኔ ዛሬ በግልጥ የምነግራችሁን ቃሎች ሁሉ በልባችሁ አኑሩ። 47ቃሎቹ ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃሎች አይደሉም፤ በእነርሱ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ፤ በምትወር ሷትም ምድር ረጅም ዘመን ትኖራላችሁ።

ሙሴ በናባው ተራራ ላይ መሞቱ

48በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 49ከኢያሪኮ ማዶ ባለው የሞዓብ ምድር፣ ከዓባሪም ተራሮች አንዱ ወደ ሆነው ወደ ናባው ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ርስት አድርጌ የምሰጣትን የከነዓንን ምድር አሻግረህ ተመልከት። 50ወንድምህ አሮን በሖር ተራራ ላይ እንደ ሞተና ወደ ወገኖቹ እንደ ተሰበሰበ ሁሉ፣ አንተም በወጣህበት በዚያ ተራራ ላይ ሙት፤ ወደ ወገኖችህም ተሰብሰብ። 51ይህ የሚሆንበት ምክንያት ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ፣ በቃዴስ በመሪባ ውሃ አጠገብ በእኔ ላይ መታመናችሁን በእስራኤላውያን ፊት ስላጐደላችሁና ቅድስናዬንም በእስራኤላውያን መካከል ስላላከበራችሁ ነው። 52ስለዚህ ምድሪቱን ከሩቅ ሆነህ ታያታለህ እንጂ፣ ለእስራኤል ሕዝብ ወደምሰጣት ምድር አትገባም።”