ዘዳግም

ምዕራፎች 33

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ሙሴ የእስራኤልን ነገዶች ባረከ

1 የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰው ሙሴ ከመሞቱ በፊት ለእስራኤላውያን የሰጠው ቃለ ቡራኬ ይህ ነው፤ 2እንዲህም አለ፦“እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሲና መጣ፤በእነርሱም ላይ ከሴይር እንደ ማለዳ ፀሓይ ወጣ፤ከፋራን ተራራ አበራላቸው፤ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጣ፤በስተ ቀኙ የሚነድ እሳት ነበር። 3በእርግጥ ሕዝቡን የምትወድ አንተ ነህ፤ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ውስጥ ናቸው።ከእግርህ ሥር ሁሉ ይሰግዳሉ፤ከአንተ ትእዛዝ ይቀበላሉ፤ 4ይህ ሙሴ የሰጠን ሕግ፣የያዕቆብ ጉባኤ ርስት ነው። 5የሕዝቡ አለቆች ከእስራኤል ነገዶች ጋር ሆነው፣በአንድነት በተሰበሰቡ ጊዜ፣እርሱ በይሹሩን ላይ ንጉሥ ነበር። 6“ሮቤል በሕይወት ይኑር፤ አይሙት፤የወገኖቹ ቊጥርም አይጒደልበት።” 7ስለ ይሁዳ የተናገረው ይህ ነው፦“እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ የይሁዳን ጩኸት ስማ፤ወደ ወገኖቹም አምጣው።በገዛ እጆቹ ራሱን ይከላከላል፤አቤቱ ከጠላቶቹ ጋር ሲዋጋ ረዳቱ ሁን! 8ስለ ሌዊም እንዲህ አለ፦“ቱሚምህና ኡሪምህ፣ለምትወደው ሰው ይሁን፤ማሳህ በተባለው ቦታ ፈተንኸው፤በመሪባም ውሃ ከእርሱ ጋር ተከራከርህ። 9ስለ አባቱና ስለ እናቱ ሲናገርም፣‘ስለ እነርሱ ግድ የለኝም’ አለ።ወንድሞቹን አልለያቸውም፤ልጆቹንም አላወቃቸውም።ለቃልህ ማን ጥንቃቄ አደረገ፤ኪዳንህንም ጠበቀ። 10ሥርዐትህን ለያዕቆብ፣ሕግህንም ለእስራኤል ያስተምራል።ዕጣን በፊትህ፣የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ በመሠዊያህ ላይ ያቀርባል። 11 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሆይ፤ ኀይሉን ሁሉ ባርክለት፤በእጁ ሥራ ደስ ይበልህ፤በእርሱ ላይ የሚነሡበትን ሽንጣቸውን ቊረጠው፤ጠላቶቹንም እንዳያንሠራሩ አድርገህ ምታቸው።” 12ስለ ብንያም እንዲህ አለ፦“የእግዚአብሔር (ያህዌ) ወዳጅ የሆነ በእርሱ ተጠብቆ በሰላም ይረፍ፤ቀኑን ሙሉ ይጋርደዋልና፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚወደውም ሰው በትከሻዎቹ መካከል ያርፋል።” 13ስለ ዮሴፍ ደግሞ እንዲህ አለው፦“እግዚአብሔር (ያህዌ) ምድሩን ይባርክ፤ድንቅ የሆነውን ጠል ከላይ ከሰማይ በማውረድ፣ከታች የተንጣለለውን ጥልቅ ውሃ በመስጠት፤ 14ፀሓይ በምታስገኘው ምርጥ ፍሬ፣ጨረቃም በምትሰጠው እጅግ መልካም ነገር፤ 15ከጥንት ተራሮች በተገኘ ምርጥ ስጦታ፣በዘላለማዊ ኰረብቶች ፍሬያማነት፤ 16ምድር በምታስገኘው ምርጥ ስጦታና በሙላቷ፣በሚቃጠለው ቊጥቋጦም ውስጥ በነበረው በእርሱ ሞገስ።እነዚህ ሁሉ በወንድሞቹ መካከል ገዥ በሆነው፣በዮሴፍ ዐናት ላይ ይውረዱ። 17በግርማው እንደ በኵር ኰርማ ነው፤ቀንዶቹም የጐሽ ቀንዶች ናቸው።በእነርሱም ሕዝቦችን፣በምድር ዳርቻ ላይ ያሉትን እንኳ ሳይቀር ይወጋል፤እነርሱም የኤፍሬም ዐሥር ሺዎቹ ናቸው፤የምናሴም ሺዎቹ እንደዚሁ ናቸው።” 18ስለ ዛብሎንም እንዲህ አለ፦“ዛብሎን ሆይ፤ ወደ ውጭ በመውጣትህ፣አንተም ይሳኮር በድንኳኖችህ ውስጥ ደስ ይበልህ፤ 19አሕዛብን ወደ ተራራው ይጠራሉ፤በዚያም የጽድቅን መሥዋዕት ያቀርባሉ።በባሕሮች ውስጥ ያለውን በተትረፈረፈ ብልጽግና፣በአሸዋውም ውስጥ የተደበቀውን ሀብት ይደሰቱበታል።” 20ስለ ጋድም እንዲህ አለ፦“የጋድን ግዛት የሚያሰፋ የተመሰገነ ነው!ክንድንና ራስን በመገነጣጠል፣ጋድ እንደ አንበሳ በዚያ ይኖራል። 21ለም የሆነውን መሬት ለራሱ መረጠ፤የአለቃም ድርሻ ለእርሱ ተጠብቆለታል።የሕዝቡ መሪዎች በተሰበሰቡ ጊዜ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የቅን ፈቃድና፣በእስራኤል ላይ የበየነውን ፍርዱን ፈጸመ።” 22ስለ ዳንም እንዲህ አለ፦“ዳን ከባሳን ዘሎ የሚወጣ፣የአንበሳ ደቦል ነው።” 23ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦“ንፍታሌም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ሞገስ ረክቶአል፤በበረከቱም ተሞልቶአል፤ባሕሩንና የደቡብን ምድር ይወርሳል።” 24ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦“አሴር ከሌሎች ልጆች ይልቅ የተባረከ ነው፤በወንድሞቹ ዘንድ ተወዳጅ ይሁን፤እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ። 25የደጃፍህ መቀርቀሪያ ብረትና ናስ ይሆናል፤ኀይልህም በዘመንህ ሁሉ ይኖራል። 26አንተን ለመርዳት በሰማያት ላይ፣በግርማው በደመናትም የሚገሠግሥ፣እንደ ይሽሩን አምላክ (ኤሎሂም) ያለ ማንም የለም። 27ዘላለማዊ አምላክ (ኤሎሂም) መኖርያህ ነው፤የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው፤‘እርሱን አጥፋው!’ በማለት፣ጠላትህን ከፊትህ ያስወግደዋል። 28ስለዚህ እስራኤል ብቻውን በሰላም ይኖራል፤የሰማያት ጠል በሚወርድበት፣እህልና የወይን ጠጅ ባለበት ምድር፣የያዕቆብ ምንጭ የሚነካው የለም። 29እስራኤል ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዳነው ሕዝብ፣እንዳንተ ያለ ማን አለ?እርሱ ጋሻህና ረዳትህ፣ የክብርህም ሰይፍ ነው።ጠላቶችህ በፍርሀት ከፊትህ ያፈገፍጋሉ፤አንተም የማምለኪያ ኰረብታቸውንመረማመጃ ታደርጋለህ።