1 እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ውደድ፤ ግዴታውን፣ ሥርዐቱን፣ሕጉንና ትእዛዙን ሁል ጊዜ ጠብቅ።
2 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤
3 በግብፅ መካከል፣ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣
4 በግብፃውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤