1 እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ውደድ፤ ግዴታውን፣ ሥርዐቱን፣ሕጉንና ትእዛዙን ሁል ጊዜ ጠብቅ።
2 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤
3 በግብፅ መካከል፣ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣
4 በግብፃውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤
5 ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፣ ለእናንተ ያደረገላችሁን ያዩት ልጆቻችሁ አልነበሩም፤
6 የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተ ሰቦቻቸው፣ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም።
7 የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።