ዘዳግም 12:10-16 NASV

10 ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል።

11 ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ።

12 እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ።

13 የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ።

14 ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝህን ሁሉ ጠብቅ፤

15 ሆኖም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል።

16 ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው።