ዘዳግም 13:10-16 NASV

10 የባርነት ምድር ከሆነው ከግብፅ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊያርቅህ ፈልጎአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።

11 ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም ማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አያደርግም።

12 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድ ትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች ባንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፣

13 ክፉ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፣ “ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ” በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፣

14 ጒዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣

15 በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ በሰይፍ ግደላቸው፤ ከተማዪቱን ከነሕዝቧና ከነቀንድ ከብቷ ፈጽሞ ደምስሳት።

16 በከተማዪቱ የተገኘውን የምርኮ ዕቃ ሁሉ በአደባባይዋ መካከል ላይ ሰብስበህ፣ ከተማዪቱን ከነምርኮዋ እንዳለ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገህ በሙሉ አቃጥል። ለዘላለም እንደ ፈረሰች ትቅር፤ ተመልሳም አትሠራ።