8 እሺ አትበለው፤ ወይም አታዳምጠው፤ አትራራለት፤ አትማረው፤ ወይም አትሸሽገው።
9 ያለማመንታት ግደለው፤ እርሱንም ለመግደል በመጀመሪያ የአንተ እጅ፣ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይነሣ።
10 የባርነት ምድር ከሆነው ከግብፅ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሊያርቅህ ፈልጎአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።
11 ከዚያም እስራኤል ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፤ ከመካከልህም ማንም እንደዚህ ያለውን ክፉ ነገር ዳግም አያደርግም።
12 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እንድ ትኖርባቸው ከሚሰጥህ ከተሞች ባንዲቱ ውስጥ እንዲህ ሲባል ብትሰማ፣
13 ክፉ ሰዎች ከመካከላችሁ ተነሥተው አንተ የማታውቃቸውን፣ “ሌሎች አማልክትን ሄደን እናምልክ” በማለት የከተማቸውን ሕዝብ እያሳቱ ቢሆን፣
14 ጒዳዩን አጣራ፤ መርምር፤ በሚገባም ተከታተል፤ ነገሩ እውነት ሆኖ ከተገኘና ይህ አስጸያፊ ነገር በመካከልህ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣