ዘዳግም 17:1-7 NASV

1 እንከን ወይም ጒድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ በእርሱ ዘንድ አስጸያፊ ነውና ለአምላክህለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አትሠዋ።

2 እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚሰጥህ ከተሞች በአንዲቱ አብሮህ የሚኖር ወንድ ወይም ሴት ኪዳኑን በማፍረስ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፉ ድርጊት ሲፈጽም ቢገኝ፣

3 ትእዛዜንም በመተላለፍ ባዕዳን አማልክትን ያመለከ፣ ለእርሱም ማለትም ለፀሓይ ወይም ለጨረቃ ወይም ለሰማይ ከዋክብት የሰገደ፣

4 አንተም ይህ መደረጉን ብትሰማ፣ ነገሩን በጥንቃቄ መርምር፤ የተባለውም እውነት ከሆነና እንዲህ ያለው አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ዘንድ መፈጸሙ ከተረጋገጠ፣

5 ይህን ክፉ ድርጊት የፈጸመውን ወንድ ወይም ሴት ወደ ከተማ ደጅ ወስደህ፣ ያን ሰው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።

6 ሞት የሚገባው ሰው፣ በሁለት ወይም በሦስት ሰዎች ምስክርነት ይገደል፤ ነገር ግን በአንድ ሰው ምስክርነት ብቻ ማንም ሰው አይገደል።

7 ሲገደልም መጀመሪያ የምስክሮቹ እጅ፣ ቀጥሎም የሕዝቡ ሁሉ እጅ ይረፍበት፤ ክፉን ከመካከልህ አስወግድ።