ዘዳግም 2:25-31 NASV

25 ከሰማይ በታች ባሉ አሕዛብ ሁሉ ላይ፣ ማስደንገጣችሁና ማስፈራታችሁ እንዲያድ ርባቸው ከዚህች ከዛሬዋ ዕለት እጀምራለሁ። ስለ እናንተ ሰምተው ይርበተበታሉ፤ ከእናንተ የተነሣም ይጨነቃሉ።”

26 ከቅዴሞት ምድረ በዳም ለሐሴቦን ንጉሥ ለሴዎን የሰላም ቃል እንዲያደርሱለት እንዲህ በማለት መልእክተኞች ላክሁ፤

27 “በአገርህ አቋርጠን እንድናልፍ ፍቀድልን፤ ከዋናው መንገድ አንወጣም፤ ቀኝም ግራም አንልም።

28 የምንበላውን ምግብ፣ የምንጠጣውንም ውሃ፣ በጥሬ ብር ሽጥልን። በእግር እንድናልፍ ብቻ ፍቀድልን፤

29 በሴይር የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ ሞዓባውያን እንዳደረጉልን ሁሉ፣ አንተም አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን እስክንሻገር ድረስ እንደዚሁ አድርግልን።”

30 ይሁን እንጂ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን እንድናልፍ አልፈቀደልንም። ምክንያቱም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) አሁን እንዳደረገው ሁሉ እርሱን በእጃችሁ አሳልፎ ለመስጠት መንፈሱን አደንድኖት፣ ልቡንም አጽንቶት ነበር።

31 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “እነሆ፣ ሴዎንንና አገሩን ለእናንተ አሳልፌ ልሰጣችሁ ተነሥቻለሁ፤ አሁንም እርሱን አሸንፋችሁ ምድሩን ለመውረስ ተነሡ” አለኝ።