ዘዳግም 29:1-7 NASV

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋር እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።

2 ሙሴ እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ፣ በፈርዖን፣ በሹማምቱ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋል።

3 እነዚያን ከባድ ፈተናዎች፣ ታምራዊ ምልክቶችና ታላላቅ ድንቆች በገዛ ዐይኖቻችሁ አይታችኋል።

4 ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም።

5 በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም።

6 ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ (ያህዌ ኤሎሂም) እንደሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።

7 ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው።