ዘዳግም 3:2-8 NASV

2 እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “እርሱን፣ መላው ሰራዊቱንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ስለ ሰጠሁህ፣ አትፍራው፤ ሐሴቦንን ይገዛ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ ያደረግህበትን በእርሱም ላይ አድርግበት” አለኝ።

3 ስለዚህ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የባሳንን ንጉሥ ዐግንና ሰራዊቱን ሁሉ እንደዚሁ በእጃችን ላይ ጣላቸው፤ እኛም አንድ እንኳ በሕይወት ሳናስቀር አጠፋናቸው።

4 በዚያን ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ የዐግ ግዛት ከሆነው፣ በባሳን ከሚገኘው ከጠቅላላው የአርጎብ ክልል ሥልሳ ከተሞች ውስጥ፣ እኛ ያልያዝነው አንድም ከተማ አልነበረም።

5 እነዚህ ከተሞች ሁሉ ከፍ ባሉ ቅጥሮች፣ በመዝጊያዎችና በመወር ወሪያዎች የተመሸጉ ነበሩ፤ እንዲሁም ቅጥር የሌላቸው አያሌ መንደሮች ነበሩ።

6 በእያንዳንዱ ከተማ ያሉትን ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቻቸውን ጭምር በማጥፋት፣ በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ እነዚህንም ፈጽመን ደመሰስናቸው።

7 ከብቱን በሙሉና ከየከተሞቻቸው የማረክነውን ሁሉ ግን ለራሳችን አደረግን።

8 ስለዚህ በዚያን ጊዜ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ ያለውን ግዛት፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ወሰድንባቸው።