ዘዳግም 3:4-10 NASV

4 በዚያን ጊዜ ከተሞቹን ሁሉ ያዝን፤ የዐግ ግዛት ከሆነው፣ በባሳን ከሚገኘው ከጠቅላላው የአርጎብ ክልል ሥልሳ ከተሞች ውስጥ፣ እኛ ያልያዝነው አንድም ከተማ አልነበረም።

5 እነዚህ ከተሞች ሁሉ ከፍ ባሉ ቅጥሮች፣ በመዝጊያዎችና በመወር ወሪያዎች የተመሸጉ ነበሩ፤ እንዲሁም ቅጥር የሌላቸው አያሌ መንደሮች ነበሩ።

6 በእያንዳንዱ ከተማ ያሉትን ወንዶቹን፣ ሴቶቹንና ልጆቻቸውን ጭምር በማጥፋት፣ በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግነው ሁሉ፣ እነዚህንም ፈጽመን ደመሰስናቸው።

7 ከብቱን በሙሉና ከየከተሞቻቸው የማረክነውን ሁሉ ግን ለራሳችን አደረግን።

8 ስለዚህ በዚያን ጊዜ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን፣ ከአርኖን ሸለቆ እስከ አርሞንዔም ተራራ ያለውን ግዛት፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የአሞራውያን ነገሥታት ላይ ወሰድንባቸው።

9 አርሞንዔምን፣ ሲዶናውያን ሢርዮን ብለው ሲጠሩት፣ አሞራውያን ግን ሳኔር ይሉታል።

10 በከፍታው ቦታ ላይ የሚገኙትን ከተሞች በሙሉ፣ ገለዓድን እንዳለ፣ እስከ ሰልካና እስከ ኤድራይ ያለውን ባሳንን ሁሉ እንዲሁም በባሳን ውስጥ የሚገኙትን የዐግ ግዛት ከተሞች በእጃችን አደረግን።