1 ከዚያም ሙሴ ወጥቶ እነዚህን ቃሎች ለእስራኤል ሁሉ ተናገረ፤
2 “እነሆ፤ መቶ ሃያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከእንግዲህ ልወጣና ልገባ አልችልም፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ‘ዮርዳኖስን አትሻገርም’ ብሎኛል፤
3 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ራሱ በፊትህ ቀድሞ ይሄዳል፤ እነዚህንም አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ አንተም ምድራቸውን ትወርሳለህ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው፣ ኢያሱም አንተን ቀድሞ ይሻገራል።
4 እግዚአብሔር (ያህዌ) የአሞራውያንን ነገሥታት ሴዎንንና ዐግን ከነምድራቸው እንዳጠፋቸው እነዚህንም ያጠፋቸዋል።
5 እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ።
6 ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”