5 እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን በፊታችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ያዘዝኋችሁን ሁሉ በእነርሱ ላይ ታደርጋላችሁ።
6 ብርቱና ደፋር ሁኑ፤ አትፍሯቸው ወይም አትደንግጡላቸው። አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ካንተ ጋር ይሄዳልና፤ አይተውህም፤ አይጥልህምም።”
7 ከዚያም ሙሴ ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻቸው ሊሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ከዚህ ሕዝብ ጋር አብረህ ስለምትገባ፣ ምድሪቱን ርስታቸው አድርገህ ስለምታከፋፍል በርታ፤ ደፋርም ሁን።
8 እግዚአብሔር (ያህዌ) ራሱ በፊትህ ይሄዳል፤ ከአንተም ጋር ይሆናል፤ ፈጽሞ አይለይህም፤ አይተውህምም፤ አትፍራ፤ ተስፋም አትቍረጥ።”
9 ሙሴም ይህን ሕግ ጽፎ፣ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) የኪዳን ታቦት ለሚሸከሙ ለሌዊ ልጆች፣ ለካህናቱና ለእስራኤል አለቆች ሁሉ ሰጠ።
10 ከዚያም በኋላ ሙሴ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዕዳ በሚተውበት፣ የዳስ በዓልም በሚከበርበት፣ በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ፣
11 እስራኤል ሁሉ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህበእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ሲታይ ይህን ሕግ በእነርሱ ፊት በጆሮአቸው ታነበዋለህ።