ዘዳግም 33:23-29 NASV

23 ስለ ንፍታሌምም እንዲህ አለ፦“ንፍታሌም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ሞገስ ረክቶአል፤በበረከቱም ተሞልቶአል፤ባሕሩንና የደቡብን ምድር ይወርሳል።”

24 ስለ አሴርም እንዲህ አለ፦“አሴር ከሌሎች ልጆች ይልቅ የተባረከ ነው፤በወንድሞቹ ዘንድ ተወዳጅ ይሁን፤እግሩንም በዘይት ውስጥ ያጥልቅ።

25 የደጃፍህ መቀርቀሪያ ብረትና ናስ ይሆናል፤ኀይልህም በዘመንህ ሁሉ ይኖራል።

26 አንተን ለመርዳት በሰማያት ላይ፣በግርማው በደመናትም የሚገሠግሥ፣እንደ ይሽሩን አምላክ (ኤሎሂም) ያለ ማንም የለም።

27 ዘላለማዊ አምላክ (ኤሎሂም) መኖርያህ ነው፤የዘላለም ክንዶቹም ከሥርህ ናቸው፤‘እርሱን አጥፋው!’ በማለት፣ጠላትህን ከፊትህ ያስወግደዋል።

28 ስለዚህ እስራኤል ብቻውን በሰላም ይኖራል፤የሰማያት ጠል በሚወርድበት፣እህልና የወይን ጠጅ ባለበት ምድር፣የያዕቆብ ምንጭ የሚነካው የለም።

29 እስራኤል ሆይ፤ አንተ ቡሩክ ነህ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዳነው ሕዝብ፣እንዳንተ ያለ ማን አለ?እርሱ ጋሻህና ረዳትህ፣ የክብርህም ሰይፍ ነው።ጠላቶችህ በፍርሀት ከፊትህ ያፈገፍጋሉ፤አንተም የማምለኪያ ኰረብታቸውንመረማመጃ ታደርጋለህ።