ዘዳግም 4:1-7 NASV

1 አሁንም እስራኤል ሆይ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፣ የአባቶቻችሁ አምላክእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ምድር እንድትገቡና እንድትወርሱ የማስተምራችሁን ሥርዐትና ሕግ ስሙ፤ ጠብቋቸውም።

2 ባዘዝኋችሁ ላይ አትጨምሩ፤ ከእርሱም አትቀንሱ፤ ነገር ግን የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ጠብቁ።

3 እግዚአብሔር (ያህዌ) በብዔልፌጎር ላይ ምን እንዳደረገ በዐይናችሁ አይታችኋል፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከመካከላችሁ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሁሉ አጥፍቶአቸዋል፤

4 አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት አላችሁ።

5 ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ (ያህዌ ኤሎሂም) ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ።

6 በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ “በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው” ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና።

7 በምንጠራው ጊዜ ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለእኛ ቅርብ እንደሆነ አማልክቱ የሚቀርቡት ሌላ ታላቅ ሕዝብ ማነው?