ዘዳግም 4:22-28 NASV

22 እኔም በዚህች ምድር እሞታለሁ፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤ እናንተ ግን ልትሻገሩ ነው፤ ያችንም መልካም ምድር ትወርሳላችሁ።

23 አምላካችሁእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን ኪዳን እንዳትረሱ ተጠንቀቁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የከለከለውን ጣዖት በማናቸውም ዐይነት መልክ ለራሳችሁ አታብጁ።

24 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚባላ እሳት ቀናተኛም አምላክ (ኤሎሂም) ነውና።

25 ልጆችንና የልጅ ልጆችን ከወለዳችሁና በምድሪቱም ላይ ለረጅም ጊዜ ከኖራችሁ በኋላ ራሳችሁን በማርከስ ማንኛውንም ዐይነት ጣዖት ብታበጁ፣ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ክፋት በማድረግ ለቊጣ ብታነሣሡት፣

26 ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ላይ ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምስክሮች አድርጌ እጠራለሁ፣ በዚያ ቦታ ብዙ ዘመን አትኖሩም፤ ፈጽሞ ትጠፋላችሁ።

27 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፤ እግዚአብሔር በሚበትናችሁ አሕዛብ መካከል የምትተርፉት ጥቂቶቻችሁ ብቻ ናችሁ።

28 እዚያም፣ ማየት ወይም መስማት ወይም መብላት ወይም ማሽተት በማይችሉ በሰው እጅ በተሠሩ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክት ታመልካላችሁ።