ዘዳግም 4:31-37 NASV

31 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሓሪ አምላክ (ኤሎሂም) ነውና፣ አይተውህም ወይም አያጠፋህም፤ ወይም ደግሞ ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።

32 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን ጀምሮ እናንተ ከመኖራችሁ በፊት ስለ ነበረው የቀድሞ ዘመን ጠይቁ፤ ከአንዱ የሰማይ ጫፍ እስከ ሌላው የሰማይ ጫፍ ድረስ ጠይቅ፤ እንደዚህ ያለ ታላቅ ነገር ከቶ ተደርጎ ወይስ እንደዚህ ዐይነት ነገር ከቶ ተሰምቶ ያውቃልን?

33 ከእሳት ውስጥ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ድምፅ እንደ እናንተ የሰማና በሕይወት የኖረ ከቶ ሌላ ሕዝብ አለን?

34 አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች ከሌላ ሕዝብ መካከል አንድን ሕዝብ የራሱ ለማድረግ የቻለ አምላክ አለን?

35 እግዚአብሔር እርሱ አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኑን፣ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን ታውቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታዩ ተደረገ።

36 ሊገሥጽህ ድምፁን ከሰማይ እንድትሰማ አደረገ፤ በምድርም ላይ አስፈሪ እሳቱን አሳየህ፤ ከእሳቱም ውስጥ ቃሉን ሰማህ።

37 አባቶችህን ከመውደዱ የተነሣና ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን ስለ መረጠ፣ ከአንተ ጋር በመሆን በታላቅ ኀይሉ ከግብፅ አወጣህ፤