1 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን፣ ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣
2 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ ከእነርሱ ጋር አትዋዋል፤ አትራራላቸውም።
3 ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤
4 ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው።