ዘዳግም 7:1-6 NASV

1 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር በሚያመጣህና ብዙዎችን፣ ከአንተ የሚበልጡ ታላላቆችና ብርቱዎች የሆኑትን ሰባቱን አሕዛብ፦ ኬጢያውያንን፤ ጌርጌሳውያንን፣ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊትህ በሚያስወጣቸው ጊዜ፣

2 አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ አሳልፎ በሰጠህና አንተም ድል ባደረግሃቸው ጊዜ፣ ሁሉንም ፈጽመህ ደምስሳቸው፤ ከእነርሱ ጋር አትዋዋል፤ አትራራላቸውም።

3 ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤

4 ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቊጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው።

5 እንግዲህ በእነርሱ ላይ የምታደርጉት ይህ ነው፤ መሠዊያዎቻቸውን አፈራርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን ቊረጡ፤ ጣዖቶቻቸውንም በእሳት አቃጥሉ።

6 አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ስለ ሆንህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የራሱ ሕዝብ፣ ርስትም እንድትሆንለት በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ መረጠህ።