ዘዳግም 9:21-27 NASV

21 ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ አበጅታችሁት የነበረውን ጥጃ ወስጄ፣ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።

22 በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሐታአዋ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አስቈጣችሁት።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከቃዴስ በርኔ ባስ ወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም።

24 እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን እንደሚያ ጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤

26 እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ (አዶናይ ያህዌ) በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ።

27 ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት።